አንድ ተማሪ እንዴት ልዩ ትምህርትን መማር ይጀምራል?

አንድ ተማሪ እንዴት ልዩ ትምህርትን መማር ይጀምራል?

የልዩ ትምህርት አገልግሎት የሚፈልጉ ተማሪዎችን ዲስትሪክቱ እንዴት ማግኘት ይችላል?

በ Individuals with Disabilities Education Act (IDEA፣ የአካል ጉዳተኞች ትምህርት አዋጅ) እና በግዛቱ የልዩ ትምህርት ህግ መሰረት፣ ዲስትሪክቶች በዲስትሪክቱ ውስጥ የሚኖሩ የልዩ ትምህርት አገልግሎቶች የሚያስፈልጋቸውን ተማሪዎች በሙሉ የመለየት አወንታዊ ግዴታ አለባቸው። ይህ ተግባር “Child Find (ልጅ ማግኘት)” ተብሎ ይጠራል። ዲስትሪክቶች አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን በመፈለግ፣ በማግኘት፣ እና እንዲገመገሙ የሚያደርጉ ፖሊሲዎች እና አካሄዶች እንዲኖራቸው ያስፈልጋል።

ልጄ ለልዩ ትምህርት እንዴት ሊገመገም ይችላል?

ለልዩ ትምህርት ግምገማ ልጅዎ ወደ ትምህርት ቤት ዲስትሪክት መምራት አለበት። የልዩ ትምህርት ምዘና ለማካሄድ፣ ዲስትሪክቱ ተማሪውን ለመገምገም መወሰን እና ከዚያም ምዘናውን ለማከናወን ከተማሪው ወላጅ ፈቃድ ማግኘት ወይም የተማሪው ወላጅ ምዘናውን እንዲያደርግ መስማማት አለበት። የትምህርት ቤቱ ዲስትሪክቶች ከተጠረጠረው ወይም ከተጠረጠረችው ተማሪ የአካል ጉዳት ጋር በተገናኘ እያንዳንዱን ጉዳዮች መገምገም አለባቸው።  ግምገማው ተማሪው ወይም ቤተሰቡ ምንም ወጪ ሳያደረግ መፈጸም አለበት። ግምገማው እንዲከወን ለማድረግ ሶስት መሰረታዊ ደረጃዎች አሉ፦

ደረጃ 1 አንድ ሰው ተማሪው እንዲመዘን ጥያቄ ማቅረብ አለበት።

ደረጃ 2 ምዘናው አስፈላጊ መሆኑን ዲስትሪክቱ መወሰን አለበት።

ደረጃ 3 የምዘና ስምምነት ለዲስትሪክቱ መሰጠት ይኖርበታል።

ለልጄ የልዩ ትምህርት ግምገማ ጥያቄ ማቅረብ እችላለሁ?

በዋሽንግተን ህግ፣ የሚከተሉት ሰዎች ወይም አካላት ተማሪው እንዲገመገም ሊያመለክቱ ይችላሉ፦

  • ማንኛውም የወላጅነት ትርጓሜን የሚያሟላ ሰው
  • የትምህርት ቤት ዲስትሪክት
  • ሌላ የህዝብ አጀንሲ
  • ስለ ህጻኑ የሚያውቁ ሌሎች ሠዎች

የግምገማ ሪፈራል እንዴት ማድረግ እችላለሁ?

1. በጽሁፍ ያቅርቡት። ሪፈራሉን የሚያቀርበው ሰው መጻፍ የማይችል ካልሆነ በስተቀር የግድ በጽሁፍ መቅረብ አለበት። ቀላል እና በእጅ የተጻፈ መሆን ይችላል። ቀኑን እና የቅጂ መዝገቦችን ማስቀመጥዎን እርግጠኛ ይሁኑ።

2. የሪፈራል ደብዳቤው የተሟላ ስለመሆኑ አይጨነቁ። መጨነቅ ያለብዎት በተቻለ ፍጥነት መጨረስ ስለመቻልዎ ነው። ሪፈራል እስካልተደረገ ድረስ ምንም ነገር አይከሰትም፣ እናም ዲስትሪክቱ ሪፈራሉን በተቀበለበት ቀን ዲስትሪክቱ እርምጃ መውሰድ ያለበትን የጊዜ ገደቦችን ያስጀምራል።

3. ትምህርት ቤቱ ሁለቱንም የ IDEA እና አንቀፅ 504 ብቁነት እንዲገመግም ይጠይቁ። ተማሪው በ IDEA ስር ለልዩ ትምህርት ብቁ ካልሆነ፣ እርሱ ወይም እርሷ በአንቀፅ 504 ስር አገልግሎቶችን ለማግኘት ብቁ ሊሆኑ ይችላሉ።

4. ልጅዎ አለበት ብለው የሚያስቡትን ችግሮች ለይተው ይግለጹ። ዲስትሪክቶች የተጠረጠረውን ተማሪ አካል ጉዳት በሁሉም አቅጣጫ መመዘን ስላለባቸው፣ ሁሉንም ችግሮች መግለጽዎን እርግጠኛ ይሁኑ። ለምሳሌ፣ ልጅዎ የማንበብ እክል እና ሊታረሙ የሚገባቸው ስሜታዊ ችግሮች እንዳለበት ካሰቡ፣ በሁለቱም እንዲመዘን ይጠይቁ።

5. ምሳሌዎችን ይጠቀሙ። ልጅዎ የአካል ጉዳት አለበት ብለው ለምን እንዳሰቡ ለመግለጽ የራስዎን ምልከታ ያካቱ። ልጅዎ እክል እንዳለበት የሚጠቁሙ ሰነዶች ካልዎት፣ ለምሳሌ ከዶክተሮች ወይም ከአእምሮ ጤና አቅራቢዎች የተፃፉ ደብዳቤዎችን ያቅርቡ።

6. ሪፈራሉን በትምህርት ቤቱ ወይም በዲስትሪክቱ ውስጥ ላለ ባለሥልጣን ነው ብለው ለሚገምቱት ሰው ይላኩ እና በፍጥነት እርምጃ ይወስዳል። ምንም እንኳን ህጉ ረፈራሉ የሚላክለትን ሰው ወይም መስሪያ ቤት በግልጽ ባያስቀምጥም፣ ይሰራበታል ብለው ለሚገምቱት ሰው መላክ ጥሩ ሃሳብ ነው። ለምሳሌ፣ ረፈራሉን ለትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ወይም የዲስትሪክቱን የልዩ ትምህርት ዳይሪክተር ሊመርጡ ይችላሉ።

ዲስትሪክቱ ረፈራሉን ለልዩ ትምህርት ምዘና ከተቀበለ በኋላ ምን ይደረጋል?

ዲስትሪክቱ ተማሪውን ለመገምገም ለመወሰን 25 የትምህርት ቀናት አለው። (በአንቀፅ 504 ውስጥ ምንም የግምገማ ጊዜ የሉም። ዲስትሪክቱ የ 504 መመዘኛ ፖሊሲ ከሌለው፣የ IDEA የግምገማ ጊዜዎች እንደመመርያ ይጠቀሙ።) ለመመዘን ሲወሰን፣ ዲስትሪክቱ በትምህርት ቤት ወይም ከወላጅ ወይም ከአሳዳጊ የሚሰጠውን የትምህርት እና የህክምና መረጃ መገምገም አለበት። ዲስትሪክቱ ለመመዘን ውሳኔ ከሰጠ በኋላ፣ ለወላጅ ወይም ለአሳዳጊ የውሳኔውን በጽሁፍ ማስታወቂያ መላክ አለበት። ዲስትሪክቱ ላለመመዘን ውሳኔ ከሰጠ፣ ስለ ውሳኔው መቃወም ይችላሉ። ከዲስትሪክቱ ጋር አለመግባባቶችን ለመፍታት የተለያዩ መንገዶችን የሚገልጸውን የዚህን እትም አንቀፅ VII ይመልከቱ።

ዲስትሪክቱ ለመመዘን ምን ፈቃድ ያስፈልገዋል?

ድስትሪክቱ ልጁን ለመጀመሪያ ጊዜ ከመገምገሙ በፊት፣ ከወላጅ ፈቃድ መጠየቅ አለበት። ወላጁ ፍቃደኛ ካልሆነ፣ ዲስትሪክቱ የወላጁን ፍቃደኛ አለመሆን ለማሳገድ ችሎት ሊጠይቅ ይችላል።

ግምገማውን ለማድረግ ዲስትሪክቱ አንዴ ፍቃድ ካገኘ ምን ይፈጠራል?

የትምህርት ቤቱ ዲስትሪክት ተማሪውን ለመመዘን 35 የትምህርት ቀናት አለው። የዋሽንግተን ህግ እንደሚገልጸው ዲስትሪክቱ አንዴ ለልዩ ትምህርት ብቁነት ግምገማ ፍቃድ ካገኘ ለ 35 የትምህርት ቀናት፦

  • ተማሪውን ሙሉ በሙሉ ይመዝናል
  • ተማሪው የአካል ጉዳት እንዳለበት ይመዝናል
  • እርሱ ወይም እርሷ ልዩ የትምህርት አገልግሎት እንደሚያስፈልጋቸው ይወስናል

ዲስትሪክቱ የወላጅን ስምምነት እስከመዘገበ ድረስ፣ ዲስትሪክቱ እና ወላጅ ለሌላ የጊዜ ገደብ ሊስማሙ ይችላሉ። ለምሳሌ፣ አንድ ወላጅ ራሱን የቻለ የትምህርት ምዘና ውጤቶችን ለመጠበቅ ጊዜውን ለማራዘም ሊስማማ ይችላል። ወላጅ ልጁን ወደ ግምገማው ለማምጣት ደጋግሞ ፈቃደኛ ካልሆነ ወይም ልጁ ወደ ሌላ ዲስትሪክት ቢዘዋወር፣ አዲሱ ዲስትሪክት ግምገማውን ለማጠናቀቅ በቂ መሻሻል እያሳየ እስካለ ድረስ ወላጅ እና አዲሱ ዲስትሪክት ግምገማውን በጊዜ ሰሌዳው ለመጨረስ ከተስማሙ የ 35ቱ የትምህርት ቀን የጊዜ ሰሌዳ ይቋረጣል።

የዋሽንግተን ግዛት የግምገማ ጊዜ ሰሌዳዎች

evaltimeline

የልዩ ትምህርት ግምገማ ረፈራል ->

ተማሪውን ለመገምገም ለመወሰን 25 የትምህት ቀናት ->

ለግምገማ የተጻፈ የወላጅ ስምምነት ->

ግምገማውን ለማጠናቀቅ 35 የትምህርት ቀናት

በግምገማው ሂደት ልጄ ቢዘዋወር ምን ይደረጋል?

ተማሪው በተመሳሳይ የትምህርት አመት ወደ ሌላ ዲስትሪክት ከተዘዋወረ፣የተማሪው የቀድሞ ትምህርት ቤት እና አዲሱ ትምህርት ቤት በመቀናጀት በተቻለ ፍጥነት የልዩ ትምህርት ምዘናውን ጨርሰው ማስተላለፋቸውን ማረጋገጥ አለባቸው። የዋሽንግተን ግዛት ተማሪው ሲመዘገብ አዲሱ ዲስትሪክት የተማሪ መረጃዎችን ማግኘት እንዲጀምር እና የተማሪው የቀድሞ ትምህርት ቤት ዲስትሪክት በ 2 የትምህርት ቀናት ውስጥ አስፈላጊውን መረጃ እና የትምህርት መዝገቦች በተቻለ ፍጥነት እንዲሰጥ ያስገድዳል።

የልዩ ትምህርት ምዘና አላማ ምንድነው?

ዲስትሪክቱ የአካል ጉዳት እንዳለበት በተጠረጠበት አቅጣጫ ሁሉ ህጻኑን መመዘን አለበት። የልዩ ትምህርት መመዘኛ ሁለት እቅድ አለው፦ 1) የብቁነት አገልግሎቶችን ለመወሰን፣ እና 2)የተማሪውን ፍላጎቶች እና ጥንካሬዎች በመለየት የግል የትምህርት ፕሮግራም እንዲሰጠው ለማድረግ። ዲስትሪክቱ በሁሉም የተጠረጠሩ የአካል ጉዳት አቅጣጫዎች የመመዘኑ እውነታ ወሳኝ፣ አስፈላጊ ነጥብ ነው። አንዳንዴ ተማሪው ከአንድ በላይ ችግሮች ሊኖርበት ይችላል። ተማሪው ለልዩ ትምህርት በአንድ አቅጣጫ ብቁ ከሆነ ዲስትሪክቱ ምዘናውን ሊያቋርጥ ይችላል። መመዘኛው በአንድ አቅጣጫ ጋር ብቻ የተያያዘ ከሆነ፣ የተማሪውን የግል ፕሮግራም ለማዘጋጀት ስለሁሉም የተማሪው ፍላጎቶች በቂ መረጃ ላይኖር ይችላል። ለልጅዎ አስፈላጊ የሆነውን የትምህርት እቅድ ለማግኘት፣ የዲስትሪክቱ የግምገማ ሁሉን አቀፍ መሆናቸውን በጥንቃቄ ለማረጋገጥ ትኩረት ይስጡ። ዲስትሪክቱ በሁሉም ሁኔታ ምዘናውን የማድረግ ግዴታ እንዳለበት ያስታውሱ።

በየትኛዎቹ ሁኔታ ሊመዘኑ ይችላሉ እንዲሁም ምን አይነት ፈተናዎች ጥቅም ላይ ይውላሉ?

ዲስትሪክቱ ልጁን በሚከተሉት ሁኔታ ሊገመግም ይችላል፦

  • ጤና (አካላዊ እና አእምሯዊ)
  • እይታ
  • መስማት
  • ማህበራዊ እና የስሜት ጤና
  • አጠቃላይ ብልሃት
  • የትምህርት ብቃት
  • ተግባቦት፣ ንግግር፣ እና ቋንቋ
  • የሞተር ችሎታ

ለምዘና የሚጠቅሙት ፈተናዎች ለሚፈተኑበት ሁኔታ ተገቢ እና ተስማሚ መሆን አለበት። ይህ ማለት ፈተናዎቹ መለካት የሚገባቸውን ሁሉንም ነገሮች በትክክል መለካት አለባቸው። ለምሳሌ፣ የ Wechsler Intelligence Scale for Children IV (የልጆች የዌችስለር ስኬል IV) (WISC IV ተብሎ የሚጠራው) በብዛት አጠቃላይ የማሰብ ችሎታን ለመመዘን የሚጠቅም ፈተና ነው። በአጠቃላይ፣ የ WISC IV ውጤቶች ለዚህ አላማ ስላልተነደፉ የልጅን የስሜት ሁኔታ ለመለካት አይጠቅሙም። ፈተናዎች እና የመመዘኛ መሳሪያዎች መመረጥ እና መተዳደር ያለባቸው ዘርን፣ ባህልን ወይም ጾታን በማይለይ መሰረት ነው። በተጨማሪም፣ ፈተናዎች እና መሳሪያዎች፣ በዚህ ለመስጠት የማይቻል እስካልሆነ ድረስ፣ በተማሪው የትውልድ ቋንቋ ወይም በሌላ የተግባቦት ስልት (እንደ ምልክት ቋንቋ) መሰጠት አለባቸው። ምን ማድረግ አለብዎት? ስለ ፈተናዎቹ ይጠይቁ። የፈተናዎቹ ቋንቋ የሚያስፈራ ቢሆንም እንኳን፣ ጥያቄ በመጠየቅ መረዳት ይችላሉ፦

  • የፈተናው አላማ፣ እና
  • የፈተናው አይነት ለልጅዎ ትክክለኛ መሆኑን።

 

ከፈታኝ ቡድኖች መካከል አንዱን ፈተናዎቹን በግልጽ ቋንቋ እንዲያብራራልዎት ይጠይቁ። የሚሰጠው ፈተና መመዘን የሚገባውን በትክክል የመመዘን ችሎታ እንዳለው እርግጠኛ ይሁኑ። ለምሳሌ፣ አንዳንድ ፈተናዎቹ ተገቢ እንዲሆኑ እድሜ፣ የማንበብ ችሎታ፣ እና የቋንቋ ችሎታ ይጠይቃሉ። ልጅዎ ለአንድ የተለየ ፈተና በጣም ትንሽ ከሆነ፣ ለፈተናው አስፈላጊ በሆነ ደረጃ ማንበብ ካልቻለ፣ ወይም ፈተናው በልጅዎ የመጀመሪያ ቋንቋ ካልተሰጠ፣ የፈተናው ውጤቶች ጠቃሚ እና ተገቢ ላይሆኑ ይችላል።

የሚፈትነው ማነው?

በተጠረጠረው አካል ጉዳት ለመፈተን ብቁ በሆኑ ባለሙያዎች ይሰጣል። የትምህርት ቤቱ የስነ-ልቦና ባለሙያዎች ፈተናውን መስጠት ይችላሉ። ነገር ግን አንዳንድ የአካል ጉዳት ሁኔታዎች ልዩ ስልጠና የወሰደ የስነ-ልቦና ባለሙያ፣ሳይካትሪስት፣ አካላዊ ቴራፒስት/የንግግር ቴራፒስት፣ የጤና ሃኪም ወይም ሌላ ባለሙያ ሰው ሊያስፈልገው ይችላል። የዲስትሪክቱ ሰራተኛ ግምገማውን መጨረስ ካልቻለ፣ ዲስትሪክቱ የምዘናውን ሂደት የሚጨርስ ባለሙያ ከውጪ ያስፈልገዋል። እነዚህ በውጪ የሚደረጉ ምዘናዎች በዲስትሪክቱ መከፈል አለባቸው። ዲስትሪክቱ በውጪ ለሚደረግ መመዘኛ ተማሪውን ወይም ወላጅ የግል ኢንሹራንስ ካለው ወይም ሌላ እርዳታ ሊጠይቅ ይችላል ተማሪው ወይም ቤተሰብ የመድህን ጥቅማ ጥቅሞችን ወይም ሌላ የድጎማ ምንጮችን፣ ዲስትሪክቱ አሁንም የውጪ ግምገማን በማዘጋጀት እና በመክፈል ተገቢውን ግምገማ መጨረስ አለበት።

ስለ ልጁ ልዩ ትምህርት ብቁነት ዲስትሪክቱ መረጃ የሚሰበስብበት ሌሎች መንገዶች ምንድን ናቸው?

ዲስትሪክቱ ስለ ተማሪው የተግባር፣ የእድገት እና የትምህርት መረጃ ለመሰብሰብ የተለያዩ የፈተና መሳሪያዎችን እና ስልቶችን መጠቀም አለበት። መረጃ መሰብሰብ የተማሪውን ግምገማ እና የቤተሰብ፣ የተንከባካቢዎች፣ እና ሌሎች ተማሪውን የሚያውቁ ሰዎች ቃለመጠይቅን ሊያካትት ይችላል። IDEA እና No Child Left Behind Act (የማንም ልጅ ከኋላ አይቅር አዋጅ) መረጃ ለመሰብሰብ የክፍል ውስጥ ግምገማዎችን አጽንኦት ይሰጣሉ። እነዚህ በክፍል ውስጥ የሚደረጉ ግምገማዎች ብዙውን ጊዜ ስርአተ ትምህርትን መሰረት ያደረጉ መለኪያዎች (CBMs) ይባላሉ። ሁሉም የግምገማ ቡድኑ አባላት እነዚህን ግምገማዎች መከለስ እንዲችሉ CBMs ከልጅዎ ጋር ጥቅም ላይ እንደዋሉ መጠየቅ አለብዎት ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ CBMs የሚጠናቀቁት በአጠቃላይ መምህር እንጂ ከልዩ ትምህርት ሰራተኞች ጋር በጋራ አይደለም።

በግምገማው አላማ ወይም ውጤት ካልተስማማሁስ?

በግምገማው ካልተስማሙ በዲስትሪክቱ ወጪ ገለልተኛ የትምህርት ግምገማ መጠየቅ ይችላሉ። በግምገማው ዙሪያ ወይም በውጤቱ ስጋት ካልዎት፣ ማድረግ የሚችሉት ነገሮች አሉ፦

  • ከዲስትሪክቱ ጋር ይነጋገሩ እና ስጋትዎን ይናገሩ። ተጨማሪ ወይም ሌላ ግምገማ እንዲደረግሎት ዲስትሪክቱን ይጠይቁ
  • ግምግማው እንዲደረግ ሌሎች አማራጮችን ይፈልጉ (ልጅዎ አሳሳቢ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለግምገማ የሚከፈል የህክምና ሽፋን አለው? ዲስትሪክቱ የውጪ ግምገማዎችን ግምት ውስጥ ማስገባት አለበት።)
  • በዲስትሪክቱ ወጪ ገለልተኛ የትምህርት ግምገማ ይጠይቁ፣ እና የገምጋሚዎቹን ዝርዝር ከዲስትሪክቱ ያግኙ
  • እንደ ሽምግልና፣ ቅሬታ፣ ወይም የችሎት ሂደት ያሉ፣ መደበኛ የግጭት አፈታት አማራጮችን ያስቡ። ስለ ግጭት አፈታት የበለጠ መረጃ ለማግኘት የዚህን እትም ክፍል VII ይመልከቱ።

“በህዝብ ወጪ ገለልተኛ ትምህርታዊ ግምገማ” ብጠይቅ ምን ይደረጋል?

ዲስትሪክቱ ጥያቄውን መመለስ ወይም ግምገማው ተገቢ መሆኑን ለማሳየት ይግባኝ ይጠይቃል። ገለልተኛ ትምህርታዊ ግምገማ ማለት የዲስትሪክቱ ተቀጣሪ ባልሆነ ብቁ በሆነ ባለሙያ የሚሰጥ ለተማሪው የሚሰጥ መመዘኛ ነው። በተጠየቀ ጊዜ፣ ዲስትሪክቱ ገለልተኛ ግምገማ የት እንደሚገኝ ለወላጆች መረጃ መስጠት አለበት። ወላጆች ማን እንደሚገመግም መምረጥ ይችላሉ። ዲስትሪክቱ ገለልተኛ ግምገማን ከተቃወመ የፍትህ ችሎት ሂደት ለመጠየቅ 15 ቀናት አሉት። ዲስትሪክቱ በ 15 ቀናት ውስጥ ችሎት ካልጠየቀ፣ ለገለልተኛ ግምገማ የመክፈል ወይም ይህ ያለክፍያ ለወላጅ ወይም ለተማሪ መሰጠቱን እርግጠኛ መሆን አለበት። የችሎቱ ሹም የዲስትሪክቱ ግምገማ ተገቢ ነው ብሎ ከወሰነ፣ ወላጁ አሁንም ገለልተኛ ግምገማ የማግኘት መብት አለው፣ ነገር ግን ዲስትሪክቱ መክፈል አይጠበቅበትም። ዲስትሪክቱ ምንም እንኳ መክፈል ባይኖርበትም የገለልተኛ ግምገማውን ውጤት ማጤን አለበት።